
የዕድር ኖርዌይ - ሕገ ደንብ / EDER NORWAY Vedtekter
ማውጫ
ይህ ቅደም ተከተል 7 ዋናዋና አንቀፆች እና 25 ናኡሳን አንቀፆች ይኖሩታል።
አንቀጽ 1 ስለማቋቋም
1.1 የእድሩ ዓላማና የተቋቋመበት ምክንያት
1.2 የእድሩ ስምና አርማ
1.3 የእድሩ ስምና አድራሻ
1.4 የእድሩ ሰልጣን
1.5 እድሩ ከዚህ በላይ በአንቀጽ 1.1 እስከ 1.4 ከተጠቀሱት ዓላማዎች ውጭ ማንኛውም ተግባር ማከናወን የተከለከለ ሲሆን ከዚህ
በታች የተዘረዘሩትንም ያካትታል።
1.6 የእድሩ ተግባር
አንቀጽ 2 የእድሩ ሥራ አስፈፃሚ አካላት
2.1 ጠቅላላ ጉባኤ
2.2 የሥራ አስፈፃሚ ምርጫ
2.3 የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
2.4 የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የሥራ ዘመን
2.5 ልዩ ልዩ ንኡስ ኮሚቴዎችና ደጋፊዎች
አንቀጽ 3 ስብሰባዎች
3.1 የእድሩ ጠቅላላ ስብሰባ
3.2 የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች
አንቀጽ 4 የአባልነት መብተና ግዴታዎች
4.1 አባልነትና መብት
4.2 አባልነትና ግዴታዎች
አንቀጽ 5 የፋይናንስ ጉዳዮች
5.1 የባንክ ሂሳብ
5.2 የመመዝገቢያና የአባላት ወርሃዊ መዋጮ ክፍያዎች
5.3 የመጠባበቂያና የስራ ማስኬጃ ወጪዎች
5.4 የሞት ክፍያ አፈፃፀም
5.5 የእድሩ ደረሰኝና የክፍያ ሰነዶች
አንቀጽ 6 ሞትን የሚመለከቱ ጉዳዮች
6.1 የእድሩ አባል ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ እና የአባልን ሞት ለማህበሩ ስለማሳወቅ
6.2 የቀብር አፈፃፀም ሃላፊነት
አንቀጽ 7 ልዩ ልዩ
7.1 የእድሩ ድህረ ገፅ
7.2 የእድሩን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ስለማቅረብ
7.3 የሂሳብ ዓመትና የሂሳብ መዛግብት ምርመራ (ኦዲት)
7.4 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ገንዘብ እና ሌላም ጉዳይ በተመለከተ ግዴታዎች
7.5 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በግል ተጠያቂ አለመሆናቸውን በተመለከተ
7.6 የእድሩን ሀብት እና ንብረት ስለማስተላለፍ
7.7 ደንቡ የሚፀናበት ጊዜ
አንቀጽ 1 የእድር ኖርዌይ ስለማቋቋም
-------------------------- በተካሄደው ስብሰባ እዚህ ደንብ መጨረሻ ላይ የተያያዘው አባሪ ላይ ስማቸውና አጭር ዘገባቸው
የተገለፀው የመስራች አባላት በሁለት ሶስተኛ አብላጫ ድምፅ ከትርፍ ነፃ የሆነ “እድር ኖርዌይ“ ከዚህ በኋላ እድሩ እየተባለ
የሚጠቀሰውን) እድር አቋቁመው፥ የተቋቋመበትን አላማ ስራ ላይ ለማዋል የመተዳደርያ ደንቡን አፅድቀዋል። ይህ እድር በኖርዌይ
ህግጋት መሰረት የተቋቋመ ማህበር ነው።
1.1 የእድሩ አላማና የተቋቋመበት ምክንያት አባላትን በስሩ በማደራጀት የሞት አደጋ በሚደርስ ጊዜ እርስ በእርስ
ለመረዳዳት በአይነቱ ልዩ የሆነ ዘዴ በመጠቀም ከእያንዳንዱ አባል ገንዘብ ለማሰባሰብና ለሟች አባል
ቤተሰብ የቀብር ወጪዎችን ለመሸፈን የሚረዳ የገንዘብ እርዳታ ለማድረግ ነው።
1.1.1 የእድሩ እቅድ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ 50 አባላትን ለመመዝገብ ነው። ይህንን ቁጥር በስድስት
ወር ውስጥ ለመሙላት ካልተቻለ የእድሩን ህልውና ለመወሰን የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ይጠራል።
1.1.2 የእድሩ ለሟች አባላት ቤተሰብ የሚያደርገው ድጋፍ መጠን የሚወሰነው በእድሩ የአባላት መጠን እና
በሚኖረው ዘላቂ አቅም ይሆናል :: ይህም ከታች ባለው ዝርዝር መነሻ ሀሳብ የሚካተት ይሆናል :: በዚህ
አንቀጽ የእድር አባል ሲባል በእድሩ ተመግቦ ወርሀዊ መዋጮ የሚከፍለውን ነው ::
1.1.2.1 የእድሩ መስራች አባላት ከምስረታ በሁዋላ ወርሀዊ ክፍያ እንዲጀመር ቦርዱ ከሚወስንበት ወር ጀምሮ በመጀመሪያው 6 ወራት የሚሰጥ ድጋፍ ከእድሩ ካዝና የአባላት አንድ ወር ወርሀዊ ክፍያ ድምር ወጪ የሚሆን ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ አባላት 300 ክሮነር በማዋጣት ተደምሮ ይሰጣል::
1.1.2.2 ከስድስት ወር በሁዋላ የእድሩ አባላት ቁጥር 100 ካልደረሰ 1.1.2.1 ያለው ክፍያ እስከ አንድ አመት የሚተገበር ሲሆን አባላት 100 ሁነው እድሩ ከስድት እስከ አንድ አመት ባለው እድሜው የአባላት የአንድ ወር ሙሉ መዋጮ ግምት እና ከእያንዳንዱ አባል የሚሰበሰብ 250 ክሮነር ጨምሮ ይሰጣል ::
1.1.2.3 የእድር አባል ቁጥር ቢያንስ 100 ሆኖ የእድሩ እድሜ ከአንድ እስከ ሁለት አመት ባለው ግዜ የሚደረግ ድጋፍ ጣሪያ የሶስት ወር የአባላት መዋጮ ድምር ይሆናል ::
1.1.2.4 የእድሩ አባላት ቁጥር 150 ( አንድ መቶ ሃምሳ) እና እድሩ ከተመሰረተ ሁለት አመት እድሜ ካስቆጠረ
እንዲሁም ምንም አይነት የገንዘብ አሰባሰብ ችግር ካልገጠመው ለአባላት 90000 ሺ ክሮነር (ዘጠና ሺህ ክሮነር) ይረዳል ::
1.1.2.5 ከሶስት አመት በሁዋል የአባላት ቁጥር የአባላት መዋጮ 10% የሚያድግ ሲሆን በዚሁ ልክ 1.1.2.3 ላይ ያለው ክፍያ 10 % በየአመቱ እያደገ ይሄዳል::
1.2 የእድሩ ስምና አርማ “እድር ኖርዌይ“ በኖርዌይ ነዋሪዎች ሲሆኑ ትውለደ ኢትዮጵያውያን ኤርትራዊያንን
ከእነሱ ጋር በባልነት በሚስትነት በስራቸው የተመዘገቡትን እና ቤተሰባቸውን እንዲያገለግል ሆኖ የተመሰረተ
ነው። እድሩ በመስራች አባላቱ የፀደቀ አርማ ይኖረዋል። እድሩ የአርማው ብቸኛ ባለቤት ነው።
1.3 የእድሩ ጽ/ቤት አድራሻ
የእድሩ ዋና ጽ/ቤት -------------------------------------------- ሲሆን ወደፊት እንደ አስፈላጊነቱ ቅርንጫፍ
ጽ/ቤት ሊመሰርት ይችላል።
1.4 የእድሩ ስልጣኖች ክልል
እድሩ አላማዎችን ለማሳካት የሚያስፈልጉት ስልጣኖች የሚኖሩት ሲሆን እነዚህ ስልጣኖች ከዚህ በታች
የተዘረዘሩትንም ያካትታል።
1.4.1 የእድሩን የአባልነት መስፈርት በመከተል በእድሩ ስር አባላትን ማሰባሰብ፥
1.4.2 የእድሩን አላማ በልዩ ልዩ ዘዴዎች አማካኝነት ማስተዋወቅ
1.4.3 የሥራ ማስኬጃ መጠባበቂያ ገንዘብ አባላት በሚመዘገቡበት ጊዜ መሰብሰብ
1.4.4 በአባል ላይ የሞት አደጋ ሲደርስ በአንቀጽ 6 እና 1 በተደነገገው ደንብ መሰረት ክፍያ መፈጸም
1.4.5 አንደየ አስፈላጊነቱ ለአባላት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ከተባባሪ አካላት ጋር በመተባበር ሴሚናሮችን
ያዘጋጃል ለምሳሌ (በጤና፣ በውርስ፣ በኖርወይ ማህበራዊ ህግጋቶች ዙሪያ)
1.5 እድሩ ከዚህ በላይ በአንቀጽ 1.4 ከተጠቀሱት ዓላማዎች ውጭ ማንኛውም ተግባር ማከናወን የተከለከለ ሲሆን
ከዚህ በታች የተዘረዘሩትንም ያካትታል።
1.5.1 የዘር፥ የፖለቲካና ሃይማኖት ነክ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ
1.5.2 ለሞት አደጋ ጊዜ ከሚፈጸመው ክፍያ ወጪ ብድርንና ተመሳሳይ የገንዘብ ነክ አገልግሎቶችን መስጠት።
1.6 የእድሩ ተግባር የሚካሄደው የእድሩን አላማ ለሟሟላት ብቻ ነው።
አንቀጽ 2 የእድሩ ሥራ አስፈፃሚ አካላት
2.1 ጠቅላላ ጉባኤ
2.1.1 የእድሩ ባለቤትነት የአባላቱ በሙሉ ሲሆን ይህም ባለቤትነት ከሚገለጽባቸው መንገዶች
ዋነኛው የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ መሳተፍ ነው።
2.1.2 ጠቅላላው ጉባኤ የሚያደርጋቸው መደበኛም ሆነ አስቸኳይ ስብሰባዎች፥
2.1.3 የእድሩን የሚያካሂዱለትን የሥራ አስፈጻሚ የቦርድ አባላትን ከአባላቱ መካከል ይመርጣል፥
2.1.4 ከሥራ አስፈጻሚው ስልጣን በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች ያስተላልፋል።
2.2 የሥራ አስፈፃሚ ምርጫ
የሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባላት ከዚህ በታች በዝርዝር በተቀመጠው የሃላፊነት መግለጫ መሰረት የእድሩን የቀን ተቀን ተግባር
ያከናውናሉ።
2.3 የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ከዚህ በታች በዝርዝር በተቀመጠው የሃላፊነት መግለጫ መሰረት የእድሩን የቀን ተቀን ተግባር
ያከናውናሉ።
2.3.1 ሊቀ መንበር
2.3.1.1 ሊቀ መንበሩ የእድሩን እንቅስቃሴዎች የመምራት ተቀዳሚ ሀላፊነት ያለበት ሲሆን የእድሩን ጠቅላላ ጉባኤ
ስብሰባዎችና የሥራ አስፈጻሚ ቦርዱን ስብሰባዎች በሊቀ መንበርነት ይመራል።
2.3.1.2 ከሶስተኛ ወገኖች ጋር እድሩን ወክሎ ግንኙነት ያደርጋል፥ እንደአስፈላጊነቱም
ሊወክል ይችላል።ይህንንን ለስራ አስፈጻሚ ቦርዱ ያሳውቃል::
2.3.2 ምክትል ሊቀ መንበር
2.3.1.1 ሊቀመንበሩ በማይኖርበት ጊዜ እርሱን ተክቶ በ 2.3.1 የተጠቀሱትን የሊቀ መንበርነትን ተግባራት ያከናውናል፥
2.3.1.2 ከሌሎች የሥራ አስፈጻሚ አባላት ጋር በመሆን ፤ለጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ የሚያስፈልጉትን ዝግጅቶች ያከናውናል፥
2.3.1.3 የእድሩ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በሚያፀድቀው መሰረት እድሩን በተለያዩ መንገዶች
የማስተዋወቅ ተግባራት ያከናውናል።
2.3.3 ፀሐፊ
2.3.3.1 ገንዘብ ነክ ያልሆኑ የእድሩን ሰነዶች ይይዛል፥
2.3.3.2 የጠቅላላ ጉባኤውንና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ቃለ ጉባኤዎች ይይዛል፥ ባመቺ ዘዴዎች
በመጠቀም ለአበላት እንዲሰራጭ ያደርጋል።
2.3.3.3 በእድሩ የሚፃፉ ገንዘብ ነክ ያልሆኑ ደብዳቤዎችን ያዘጋጃል።
2.3.3.4 የእድሩን ድረ ገጽ እንቅስቃሴ ይመለከታል።
2.3.4 ገንዘብ ያዥ እና ንብረት ሀላፊ
2.3.4.1 በእድሩ የባንክ ሂስብ ወርሀዊ ክፍያ መግባቱን ይከታተላል።
2.3.4.2 የእድሩ ለእለት ተእለት የሚያስፈልግ ገንዘብ በመያዝ በውሳኔዎች መሰረት ክፍያ እና ግዢ ያከናውናል::
2.3.4.3 የእድሩን ቁዋሚ ንብረት ይመዘግባል ይቆጣጠራል በአግባቡ ለአገልግሎት እንዲውሉ ያደርጋል ሰነዶችን
በአግባቡ አቅርቦ ያወራርዳል ለሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ያቀርባል።
2.3.5 የሂሳብ ሹም
2.3.5.1 የአባላትን ዝርዝር ወቅታዊ አድርጎ ይይዛል።
2.3.5.2 አባላት የሚፈለግባቸውን ክፍያዎች በወቅቱ መክፈላቸውን ይከታተላል። ባልከፈሉትም ላይ ተገቢውን
እርምጃ እንዲወስድ ለሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ያቀርባል።
2.3.5.3 የእድሩን ወርሃዊ የሂሳብ መግለጫ ዘገባ አዘጋጅቶ ለሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ያቀርባል። የሂሳብ ዘገባው
በየሶስት ወሩ በስራ አስፈጻሚው ፀድቆ ለአባላት ዝግጁ እንዲሆን ይደረጋል።
2.3.6 የውስጥ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ተጠሪነቱ ለጠቅላላው ጉባኤ ብቻ ሲሆን፥
2.3.6.1 የሂሳብ ስራውና የሰነድ አያያዙ በትክክል መሆኑን ያረጋግጣል።
2.3.6.2 በየሶስት ወራት የሂሳብ ምርመራ በማድረግ ለስራ አስፈጻሚው ኮሚቴ የተጠቃለለ ዘገባ ያቀርባል። ለራሱም
ኮፒ በማስቀረት እንደአስፈላጊነቱ በዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያቀርባል።
2.3.6.3 የህግና ሥነ ስርአት አማካሪ ከእድሩ አባላት በሙያቸው እና ስነምግባር በክፍሉ ቢያገለግሉ የእድሩ ቦርድ
ያመናባቸውን በመመልመል በሙሉ ድምጽ ሲስማማ በክፍሉ እንዲሰሩ ያደርጋል :: ክፍሉ የሚከተሉትን ስራ ይሰራል ::
2.3.6.3.1 የህግ ነክ ጉዳዮችን ያማክራል
2.3.6.3.2 ከአባላት የሚነሱ ስነስርአት እና ህግ ነክ ጉዳዮችን ይመረምራል መፍትሄ ሀሳብ ለስራ አስፈጻሚው ቦርድ
ያቀርባል ::
2.3.6.3.3 ከቦርዱ ጋር ቢያንስ በ 2 ወር አንዴ ስብሰባዎችን ይሳተፋል ::
2.3.7 የሕዝብ ግንኙነት የሕዝብ ግንኙነት መሪው ሃላፊነት እንደሚከተለው ይሆናል፥
2.3.6.1 በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወጣው መመርያ መሰረት አባላትን መመልመል።
2.3.6.2 የእድሩን ድረ ገጽ ማካሄድ።
2.3.6.3 የሕዝብ ግንኙነት ማስፋፋት።
2.3.8 የሌሎች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት
ቀሪዎች የሥራ አስፈጻሚ አባላት ተግባራት እንደ አስፈላጊነቱ በእድሩ ሊቀመንበር ወይም በኮሚቴ የሚወሰኑ ይሆናሉ።
2.4 የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የሥራ ዘመን
2.4.1 የሥራ አስፈጻሚ ሊቀ መንበርና ፀሐፊ የሥራ ዘመን 4 ዓመት ሲሆን ሌሎች ቦርድ አባላት ለ???
ተከታታይ ዓመታት ያገለግላሉ።
2.4.2 የሥራ አስፈጻሚ አባላት በተከታታይ ለማገልገል የሚችሉት ለሁለት ዙር ተከታታይ የሥራ ዘመናት
ነው። ሆኖም እነዚህ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ወደፊት ሊጠቆሙና ሊመረጡ ይችላሉ።
2.4.3 አንድ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል የእድሩን አላማ የሚቃወም ወይንም ህጋዊ ድርጊትን የሚቃወም
ተግበር ሲፈጽም ቢገኝ በተቀሩት የሥራ አስፈጻሚ አባላት ሙሉ ስምምነትና ድምፅ የሥራ
ዘመኑን ሳይጨርስ ከሥራ ሊታገድ ይችላል። ታጋጁ የእግዱ ህጋዊነት በሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ
እንዲታይለትና ውሳኔ እንዲሰጠው መጠየቅ ይችላል።
2.4.4 የእግዱ ውሳኔ በሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ አግባብ ሆኖ ከተገኘ የሚመለከተው አባል ለዘለቄታው
ከሥራ አስፈጻሚ አባልነቱ ይሰናበታል። ሆኖም በአንቀጽ 4.2 መሰረት ከእድሩ ካልተሰናበተ
በአባልነቱ ይቀጥላል።
2.5 ልዩ ልዩ ንኡስ ኮሚቴዎችና ደጋፊዎች
2.5.1 የቡድን መሪዎች
አባላት እንደሚኖሩበት ሰፈር ቅርበት በቡድን ተደራጅተው የቡድን መሪያቸውን ይመርጣሉ
እንደ አስፈላጊነቱም የመረጡትን አሰናብተው በምትኩ ሌላ ይመርጣሉ። እያንዳንዱ ቡድን
እስከ 20 አባላት ሊኖሩት ይችላል። የቡድን ተጠሪ ተገባራት ከዚህ የሚከትሉት ይሆናል፥
2.5.1.1 በስሩ የሚገኙ አባላት እድሩ የሚፈልግባቸውን ክፍያዎችና መዋጮዎች በወቅቱ
ማከናወናቸውን እየተከታተለ ገንዘቡን መሰብሰብና ለማህበሩ ገንዘብ ያዥ
በተቀበለ በአስር ቀናት ውስጥ ከከፋዮች የስም ዝርዝር ጋር በደረሰኝ ማስረከብ፥
2.5.1.2 በሥሩ ከሚገኙ አባላት መካከል ሰው ሲሞት ሁኔታውን ለእድሩ ፀሐፊ
ማሳወቅ፥
2.5.1.3 የሟች የቤተሰብ እንደራሴ ጋር በመሆን የሀዘንና የቀብር ማስፈጸሚያ ገንዘቡን
በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሰው ከእድሩ ጽ/ቤት ጋር ተባብሮ መስራት
2.5.1.4 በስሩ ላሉት አባላት ከእድሩ ጽ/ቤት የሚደርሰውን መረጃ ማስተላለፍና ከኣባላት
የሚደርሱትን መረጃዎችም ሆነ ጥያቄዎች ወደ ሥራ አስፈጻሚው ቦርድ
ማስተላለፍ
2.5.1.5 በስሩ የሚገኙ አባላትን አድራሻዎችና ስልክ ቁጥሮች መዝግቦ መያዝና
ወቅታዊነታቸውን የተጠበቀ ማድረግ፥ እንዲሁም ለውጦች ሲኖሩ ለየእድሩ
ጽ/ቤት ማስተላለፍ እና ጥሪ ሲደርሰው በሥራ አስፈጻሚው ስብሰባዎች ላይ
መገኘት።
2.5.2 አማካሪዎችና ድጋፍ ሰጭዎች
2.5.2.1 የሥራ አስፈጻሚው ቦርድ ለአጭር ጊዜም ሆነ ለረጅም ጊዜ ተግባራትን
በማከናወን እና ምክሮችን በመለገስ የሚያገለግሉት ሰዎች ከአባላት መካከል
ሊሰይም ይችላል።
2.5.2.2 አማካሪ ወይም ድጋፍ ሰጭ ሰው በሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ወይም በማህበሩ ሊቀ
መንበር ውሳኔ ሊሰናበትና በምትኩ ሌላ ሊተካ ይችላል።
አንቀጽ 3 ስብሰባዎች
3.1 የማህበሩ ጠቅላላ ስብሰባዎች በዓመት አንድ ጊዜ ይደረጋል።
3.1.1 አባላት በጠቅላላ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ሰላሳ (30) ቀናት ቀደም ብሎ ጥሪ እንዲደረግላቸው
ይደረጋል። ጥሪው የሚተላለፈው በቡድን መሪዎቻቸው አማካይነት፥ በማህበሩ ድረ ገጽ፥ በስልክ፥
በኢሜል ወይም በፖስታ ይሆናል።
3.1.2 ከግማሽ በላይ አባላት ሲገኙ ምልአተ ጉባኤ ይሆናል።
3.1.3 በመጀመሪያው ጥሪ ምልዓተ ጉባኤ ካልተገኘ ስብሰባው ይበተንና ለሁለተኛ ጊዜ ስብሰባ
ይጠራል። በሁለተኛው ስብሰባ ምልዓተ ጉባኤ ባይሞላም በተገኘው አባላት ብቻ ስብሰባው ሊካሄድ ይችላል።
3.1.4 ውሳኔዎች ስብሰባ ላይ በተገኙ አባላት በድምፅ ብልጫ ያልፋል። ይሁንና ድምፁ የሚሰጥበት
ጉዳይ የማህበሩን ዓላማዎች መለወጥን ወይም ማህበሩን ማፍረስ የሚመለከት ጉዳይ ከሆነ ውሳኔዎች የሚያልፉት በአባላቱ
ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ብቻ ነው።
3.1.5 የድምፅ አሰጣጡ ውጤት እኩል ከሆነ ሊቀ መንበሩ ሁለተኛ የድምፅ ድጋፉን የሰጠበት ውሳኔ ያልፋል
3.2 የሥራ አስፈጻሚው ቦርድ ስብሰባዎች
3.2.1 የሥራ አስፈጻሚው ቦርድ መደበኛ ስብሰባዎች በ1 ወር አንድ ጊዜ ይካሄዳሉ።
3.2.2 አስቸኳይ የስራ አስፈጻሚ ስብሰባ እንደአስፈላጊነቱ በሊቀመንበሩ አማካይነት ሊጠራ ወይም አምስት
የሥራ አስፈጻሚ አባላት ስብሰባ እንዲደረግ ሲጠይቁ ሊጠራ ይችላል።
3.2.3 የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ስብሰባዎች ላይ አምስት የቦርዱ አባላት ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይሆናል።
3.2.4 የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ስብሰባዎች ውሳኔዎች የሚተላላፉበት በአብላጫ ድምፅ ይሆናል።
3.2.5 ሊቀ መንበሩና ም/ሊቀመንበሩ በማይገኙበት ጊዜ የተገኙት አባላት ጊዜያዊ ሊቀ መንበር
ከመሀከላቸው ይመረጣሉ።
አንቀጽ 4 የአባልነት መብትና ግዴታዎች
4.1 አባልነትና መብት
4.1.1 በኖርዌይ ቋሚ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጲያዊ እና ኤርትራዊ ወይም ከኢትዮጲያዊ ወይም ኤርትራዊ ጋር
በጋብቻ የተሳሰረ እንዲሁም እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ማንኛውም ግለሰብ አባል መሆን ይችላል።
ሆኖም ሁሉም አባላት የአባልነት ማጣሪያ መለኪያውን ማለፍ አለባቸው። ይህ ማጣሪያ ምግባርንና ፀባይን
የሚመለከት እንጂ ከሀይማኖት ከፖለቲካ ከእድሜ ጋር አይገናኝም።
4.1.2 ማንኛውም በ 4.1.1 የተጠቀሰውን የእድሩን የአባልንት መስፈርት የሚያሟላ ግልሰብ በእድሩ
ድህረ ገፅ ላይ ያለው የአባልነት መመዝገቢያ ፎርም ሞልቶና ፈርሞ አባል መሆን ይችላል።
4.1.3 ከ18 ዓመት በታች የሆኑት ልጆች በወላጆቻቸው አማካይነት ተፈላጊውን የአባልነት ክፍያ
በመክፈል አባል መሆን ይችላሉ። ሆኖም 18 ዓመት እስከሚሆናቸው ድረስ የድምፅ መስጠት
መብት አይኖራቸውም።
4.1.4 አመልካች በእድሩ ዓላማዎች የሚያምንና የመተዳደሪያ ደንቡንም የተቀበለ መሆን አለበት።
4.1.5 አመልካቹ አባልነቱ በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት የሚጠበቅበትን ክፍያዎች ለመፈፀም የተዘጋጀ
መሆን አለበት።
4.1.6 አመልካቹ በኖርዌይ ቋሚ ኗሪ መሆኑን ለማረጋገጥ ህጋዊ መታወቂያና ሌሎች መረጃዎችን በተጠየቀ
ጊዜ ለማቅረብ ዝግጁና ፈቃደኛ መሆን አለበት።
4.1.7 ማመልከቻው ታይቶ አስፈላጊውን መስፈርቶች ካሟላና አስፈላጊው ክፍያዎች ከተከፈሉ በኋላ
አመልካቹ አባልነቱ ተረጋግጦ የአባልነት መታወቂያ ይሰጠዋል።
4.2 አባልነትና ግዴታዎች
4.2.1 ከአባልነት ስለመሰናበት
4.2.1.1 በእድሩ ደንብ መሰረት የሚፈለጉበትን ክፍያዎች ለተከታታይ ፫ ወራት ካልከፈለ አና
ከቦርዱ ማስጠንቀቂያ ደርሶት በአንድ ወር ውስጥ ካልከፈለ
4.2.1.2 የእድሩን ዓላማዎች የሚፃረሩ ተግባራት መፈፀሙ በቦርዱ አባላት ሲታመንበት
4.2.1.3 ኖርዌይን ለዘለቄታው ለቆ ሲሄድ
4.2.1.4 በራሱ ፈቃድ እድሩን መልቀቁን በጽሁፍ ለእድሩ ሲገልጽ
4.2.2 ማንኛውም አባል በራሱ ፈቃድ ሆነ በ 4.2.1 በተጠቀሱት ምክንያቶች ከአባልነት ሲሰናበት ምንም
አይነት ክፍያ ወይም ጥቅም ከእድሩ የመጠየቅ መብት የለውም
4.2.3 ማንኛውም አባል ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በአንዱ እድሩን ሲለቅ ወይም ሲሰናበት
የእድሩን መታወቂያ መመለስ አለበት።
4.2.4 በራሱ የግል ምክንያት ካቋረጠና በሚያቋርጥበት ጊዜ በደንቡ መሰረት እድሩ የሰጠውን መታወቂያ
ከመለሰ በሌላ ጊዜ አባል ለመሆን ከፈለገ እንደ አዲስ አባል እድሩ ሊቀበለው ይችላል
4.2.5 ማንኛውም አባል አድራሻውን ሲለውጥ አዲሱን አድራሻ በፅሁፍ ለቡድን መሪውና ለእድሩ ፅ/ቤት
ማሳወቅ አለበት።
አንቀጽ 5 የፋይናንስ ጉዳዮች
5.1 የባንክ ሂሳብ
5.1.1 እድሩ በኖርዌይ ካሉት የባንክ ተቋማት በስሙ አንድ ወይም የተለያዩ አካውንት እንደአስፈላጊነቱ
ይኖረዋል።
5.1.2 የባንክ አካውንቱን ለመክፈት የሚፈርሙት ሊቀ መንበሩ፥ ም/ሊቀመንበሩና ሂሳብ ሀላፊው ናችው።
5.1.3 ማንኛውም ዓይነት የገንዘብ ክፍያዎችን ውሳኔ የሚሰጠው የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ነው
5.1.4 ማንኛውም ዓይነት የገንዝብ ክፍያ የሚደረገው ከላይ በቁጥር 5.1.2 የመፈረም ስልጣን
ከተሰጣቸው ሁለት የስራ አስኪያጅ ኮሚቴ ሲፈርሙበት ብቻ ነው።
5.2 የመመዝገቢያና የአባላት ወርሃዊ መዋጮ ክፍያዎች
5.2.1 የመመዝገቢያ ክፍያዎች
5.2.1.1 አንድ ሰው የእድሩ አባል ለመሆን በሚመዘገብበት ጊዜ በጠቅላላው kr. 1000,- ይከፍላል :: ክፍያውን በሁለት ተከታታይ ወር ማጠናቀቅ ይችላል።
5.2.2 የአባላት ወርሃዊ መዋጮ
5.2.2.1. ማንኛውም የእድሩ አባል በቤተሰብ ( ባል ሚስት እና ልጆች ) በአንድ አድራሻ ተመዝግበው የሚኖሩ ሲሆኑ በወር 250 ክሮነር ወርሃዊ መዋጮ ይከፍላል
5.2.2.2. በአንድ አድራሻ ተመዝግበው የሚኖሩ ባለትዳሮች ወይንም ፍቅረኛሞች በወር 200 ክሮነር ይከፍላሉ::
5.2.2.3 ብቻቸውን የሚኖሩ ግለሰቦች በወር 150 ክሮነር ይከፍላሉ
5.2.2.4 እድሜያቸው ከ 18 - 25 ድረስ ያሉ እና ወላጆቻቸው ጋር የሚኖሩ የራሳቸው ገቢ ከሌላቸውው ከወላጆቻቸው ጋር እንደ አባል ሊመዘገቡ ይችላሉ::
5.3 የመጠባበቂያና የስራ ማስኬጃ ወጪዎች
5.3.1 እድሩ ሶስት ተከታታይ የአባላት ሞት በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢያጋጥም አድሩ ክፍያውን
ለመፈጸም እንዲችል ቢያንስ ክሮነር 20000 ሺህ የመጠባበቂያ ገንዘብ ሊቀረው ይገባል ። ይህ
መጠባበቂያ ገንዘብ ባነሰ ግዜ አባላት ድጋፍ አንዲያደርጉ ጥሪ ይደረጋል፧፧ የአባላት ቁጥር ሲጨምር የመጠባበቂያውም ገንዘብ ይጨምራል።
5.3.2 የእድሩ የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች የሚሸፍነው እያንዳንዱ አባል በምዝገባ ወቅት ከከፈሉት 1000,- መዋጮ ይ ነው።
ይህ ወጪ በስራ አስፈጻሚ ቦርዱ እየታየ ሊጨምር ይችላል።
5.4 የሞት ክፍያ አፈፃፀም
5.4.1 የማስተዛዝኛ ክፍያ
5.4.1.1 አባል የሆነ ግለሰብ በሞት በሚለይበት ጊዜ ከእድሩ አካውንት ለሟች
ቤተሰብ ከሚከፈለው ሙሉ ክፍያ ላይ 20% ወጪ ተደርጎ ለአስቸኳይ
ማስተዛዘኛ ለቤተሰብ ተወካይ ይከፈላል።
5.4.1.2 ቀሪው 80% የሚከፈለው የአባሉ መሞት በማስረጃ ሲረጋገጥ ይሆናል።
1) የሞት ማረጋገጫ ሰነድ
2) የ 3 ወይንም ከ 3 በላይ የሰዎች ምስክርነት
5.5 እድሩ ደረሰኝና የክፍያ ሰነዶች
5.5.1 የእድሩ ሥምና አርማ የሰፈረባቸው የገንዘብ መሰብሰቢያና የመክፈያ ደረሰኞች የሥራ አስፈጻሚ
ኮሚቴ በሚወስነው አይነትና መጠን ይዘጋጃል
5.5.2 የእድሩ የገንዘብ ያዥ ለቡድን መሪዎችና ለተመረጡት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ጣቢያዎች በአባሎቹ
መጠን ቆጥሮ ደረሰኞች የማስረከብ ግዴታ አለበት። ገንዘብ ያዥው ለደረሰኞች መዝገብ አያያዝ
ሀላፊነት ያለበት ሲሆን በጥንቃቄ መሰራጨታቸውንም ያረጋግጣል።
አንቀጽ 6 ሞትን የሚመለከቱ ጉዳዮች
6.1 የእድሩ አባል ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ እና የአባልን ሞት ለእድሩ ስለማሳወቅ
6.1.1 የሟች ቤተሰብ ተወካይ ለሰራ አስኪያጅ ኮሚቴው ያሳውቃል
6.1.2 የሰራ አስኪያጅ ኮሚቴው መልእከቱ እንደደረሰው በአንቀጽ 5.4.1.1 የተገለጸውን ክፍያ
ይፈጽማል
6.1.3 አባሉ የሞተው በኖርዌይ ውስጥ ከሆነ ለቀብር ማስፈጸሚያ ክፍያ የእድሩ አባል ከዚህ ዓለም
በሞት መለየቱ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ በ 10 ቀናቶች ውስጥ በአንቀጽ
5.4.1.1 እና 5.4.1.2 የተገለጸውን ክፍያ ይፈጽማል
6.1.4 አባሉ የሞተው ከኖርዌይ ውጭ ከሆነ እጅግ ቢዘገይ በሰላሳ (30) ቀናት ውስጥ የሟች ቤተሰብ
ተወካይ ለሰራ አስኪያጅ ኮሚቴው ያሳውቃል:: የሰራ አስኪያጅ ኮሚቴው የደረሰው መልክት
ትክክለኛንቱን ካርጋገጠ በኋላ በ 10 ቀናቶች ውስጥ ለሟች ቤተሰብ በአንቀጽ
5.4.1.1 እና 5.4.1.2 የተገለጸውን ክፍያ ይፈጽማል
6.1.5 እድሩ በአንቀጽ 5.4.1.2 ላይ የተገለጸውን የሞት ማረጋገጫ ሰነድ በቂ ሆኖ ካላገኘው ክፍያውን
አይፈፅምም።
6.1.6 በንዑስ አንቀጽ 6.1 የተገለጸው የጊዜ ገደብ ካለፈ በኋላ የሚቀርብ የሞት ሪፖርትና የሞት የሀኪም
የምስክር ወረቀት ለሟች ክፍያ አያስገኝም።
6.1.7 ሟች ሌላ የቅርብ ዘመድ የሌለው ከሆነ ማንኛውም የእድሩ አባል መሆኑን የሚያውቅ ሰው አባሉ መሞቱን ባወቀ
በ7 ቀናት ውስጥ የሟቹን ስም እና ከተቻለም የመታወቂያ ቁጥሩን ጨምሮ ለእድሩ ጽ/ቤት መግለፅ ይቻላል።
ይህ በሚሆንበት ጊዜ ማህበሩ ሟቹ በእርግጥ አባል መሆኑን አረጋግጦ ከእድሩ ሂሳብ ወጪ ተደርጎ የቀብር
ስነስርአቱን ያስፈጽማል። ማንኛውም ለቀብር ማስፈጸሚያ የወጡ ወጪዎችን በሕጋዊ ማረጋገጫ ሰነድ ያረጋግጣል።
6.1.8 የእድሩ ጽ/ቤት የአንድ አባል ከዚህ ዓለም በሞት መለየት መረጃ እንደደረሰው የመረጃውን እውነተኛነት
ካረጋገጠ በህዋላ ሁኔታውን በአስቸኳይ ለእድሩ አባላት በተመቸ የመረጃ መረብ ያሳውቃል።
6.1.9 በተጨማሪ የእድሩ ጽ/ቤት ከሟች የቤተሰብ ወኪል ተጽፎ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የፀደቀ ወይም የተሻሻለ አጭር
የሕይወት ታሪክና (የቤተሰብ ወኪል ከፈቀደ) ከሟች ፎቶግራፍ ጋር በእድሩ ድረ ገጽ ላይ እንዲለጠፍ ያደርጋል።
ሟች የቤተሰብ ወኪልም ሆነ ሌላ የቅርብ ዘመድ ከሌለው የእድሩ ጽ/ቤት ያወቀውን ያህል የህይወት ታሪክ ያዘጋጃል።
6.2 የቀብር አፈፃፀም ሃላፊነት
6.2.1 የሟች የቤተሰብ እና ወኪል የቀብር ስርዓቱን የማቀናበር ሀላፊነት አለባችው። ሆኖም በተሰብ
ወይንም የቤተሰብ ወኪል እድሩን እርዳታ በጠየቀ ጊዜ እርዳታ ይደረግለታል።
6.2.2 ቤተሰብ የሌለው አባል በሞት በሚለይበት ጊዜ፥
6.2.2.1 የእድሩ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአስቸኳይ ለሟች እንደቤተሰብ ሆኖ
የሚያገለግል ኮሚቴ ያዋቅራል።
6.2.2.2 የተዋቀረው ኮሚቴ በእድሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አመራር ሰጪነት ቀብሩ
እንዴት መፈጸም እንዳለበት የስራ ዝርዝር በማውጣት ሙሉ ዝግጅቱን እስከ
ፍጻሜው ድረስ ከሌላው አባል ባልተለየ መልኩ ሥርዓቱ እንዲፈጸም ያደርጋል።
የሟች አሰከሬን ወደ አገርቤት መላክ ካለበት ጊዝያዊው ኮሚቴው የመላኩን ሂደት ያስፈጽማል::
የእድሩ ጽ/ቤት ስለቀብሩ አፈጻጸም ወይም የአስከሬን ሽኝት ሂደት አፈጻጸም
ዝርዝር በእድሩ ድህረ ገጽ ላይ ለአባላቱ ያስታውቃል።
አንቀጽ 7 ልዩ ልዩ
7.1 የእድሩ ድህረ ገፅ
7.1.1 እድሩ ከሚጠቀምባቸው የመገናኛ መረቦች ውስጥ ዋነኛው የእድሩ ድህረ ገጽ ነው:: አላማውም
አባላትን አግባብ ያላቸውን መረጃዎችና ሰነዶች ከድህረ ገጹ ለማውረድ (download ለማድረግ)
እንዲችሉ ነው:: የድህረ ገጹ ሥምና አድራሻ ለአባላት ይገለፃል። ከድህረ ገጹ በተጨማሪም ኢሜል፥
ደብዳቤና ሰልክ የመገናኛ ዘዴዎች ይሆናሉ።
7.1.2 ድህረ ገጹ እድሩን ከሚመለከቱ ማስታወቂያዎች ውጭ የማንንም የፖለቲካ፥ የሃይማኖት፥ የግል
ድርጅት፥ ወይም የግለሰብን ጥቅም ሊያስከብር የሚችል ማንኛውንም አይነት ማስታወቂያ አያስተናግድም።
7.2 የእድሩን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ስለማቅረብ
7.2.1 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይህ ደንብ መሻሻል ይገባዋል ብሎ ሲያምን የማሻሻያ ሀሳቦችን ለጠቅላላው
ጉባኤ ማቅረብ ይችላል።
7.2.2 ማንኛውም የእድሩ አባል የአባላቱን ሁለት ሶስተኛ የድጋፍ ፊርማ በማሰባሰብ የእድሩን መተዳደሪያ
ደንብ የማሻሻያ ሃሳቡን ለእድሩ ሊቀ መንበር በማቅረብ ለሚቀጥለው ስብሰባ ውይይት
እንዲካሄድበት መጠየቅ ይችላል።
7.3 የሂሳብ ዓመትና የሂሳብ መዛግብት ምርመራ (ኦዲት)
7.3.1 የእድሩ የሂሳብ ዓመት በጃንዋሪ 1 ጀምሮ በዲሴምበር 31 ይጠናቀቃል።
7.3.2 የማህበሩ የሂሳብ መዛግብት በውጭ ኦዲተር በዓመት አንድ ጊዜ ተመርምሮ ሪፖርቱ ለስራ አስኪያጅ
ኮሚቴው ይቀርባል።
7.3.3 የማህበሩ የሂሳብ አመት በተጠናቀቀ በ3 ወራት ውስጥ የሂሳብ መዝገቡ ምርመራ መጠናቀቅ
አለበት። የምርመራውም ውጤት በውጭ ኦዲተሩ ለእድሩ ጠቅላላ ጉባኤ ይቀርባል።
7.4 የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ገንዘብ እና ሌላም ጉዳይ በተመለከተ ግዴታዎች
7.4.1 የእድሩን ገንዘብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ሥር ሆነው በሚያገለግሉት አባላት
ለማንኛውም አይነት የግል ጉዳይ ማዋል አይቻልም። ይህንን ደንብ የተላለፈ በሕግ ያስጠይቀዋል።
7.4.2 የእድሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምንም አይነት ክፍያ ሳይደረግላቸው በሙሉ ፈቃደኝነት
የሚያገለግሉ ግለሰቦች ናቸው። ይህን የበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸውን በሚሰጡበት ወቅት ከእድሩ
ሥራ ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ ስህተቶች በግል ተጠያቂ አይሆኑም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በአንቀጽ
7.4.1 የተጠቀሰውን ደንብ ተላልፎ የተገኘ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ላይ ተፈጻሚ አይደለም።
7.4.3 የእድሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከአባላት የሚሰጡትን መረጃዎች የግል፣ የገንዘብ ወይም የንግድ
ጉዳዮች በአጠቃላይ በኖርዌይ ህግ መሰረት ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው።
7.4.4 በእድር ኖርዌይ መርህ መሰረት ማንኛውም አይነት አድሎ በእድሩ አባላት መካከል መኖር የለበትም።
7.6 የእድሩን ሀብት እና ንብረት ስለማስተላለፍ
እድሩ አባላት ውሳኔ ወይም በሌላ በማንኛውም ምክንያት እድሩ ሥራውን እንዲያቆም ቢገደድ የማህበሩ እዳዎች ከተከፈሉ
በኋላ የሚቀረው የእድሩ ሀብትና ንብረት የኖርዌይ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ለአባላት ተመላሽ እንዲሆን ይደረጋል።
7.7 ደንቡ የሚፀናበት ጊዜ
ይህ የመተዳደሪያ ደንብ መስራች አባላት በሁለት ሶስተኛ አብላጫ ድምጽ ካፀደቁበትና ፊርማቸውን ካሰፈሩበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል።